Saturday, November 9, 2013
Friday, November 8, 2013
ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ቤት ውስጥ ሆነው ይጠይቁት የነበረውን ጥያቄ አሁን አደባባይ ወጥተዉ መጠየቅ መቻላቸዉ ዲሞክራሲያዊ ስኬት ነው ያለዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ በችርቻሮ የሚሰጥ የወያኔ ችሮታ ይመስል ሰልፉ በየእሁዱ የሚቀጥል ከሆነ ሰልችቶናልና እንከለክላለን ማለቱ እንደ ግንቦት 7 እምነት ቀድሞዉንም ቢሆን ወያኔ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ይቻላል ብሎ ፈቃድ የሰጠዉ ለዲሞክራሲ ካለዉ እይታና እራሱ የጻፈዉን ህገ መንግስት ተከትሎ ሳይሆን እርዳታ ሰጪ ምዕራባዉያን አገሮችን ለማስደሰት ብቻ ነዉ።
አገር ዉስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተቀናጀ ትግል ማድረግ በመጀመራቸዉ ክፉኛ የተደናገጠዉ ወያኔ “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” አንደሚባለዉ እነዚህን ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ፤ እኩልነትና፤ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የሚታገሉትን ፍጹም ህዝባዊና ፍጹም ሰላማዊ የሆኑ ድርጅቶች ለማጥፋት ሰበብ ሲፈልግ የተለመደዉን ግንቦት 7 የሚል ዘፈኑን መዝፈን ጀምሯል። የወያኔ አገዛዝ በአፉ አንደሚናገረዉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስብና የሚጨነቅ ከሆነ ማድረግ ያለበት ከኢትዮጵያ ህዝብ ለሚቀርብለት ጥያቄ ተገቢዉን ምላሽ መስጠት ብቻ ነዉ። አለዚያ ህዝብ ጥያቄ ባነሳና ለመብቱና ለነጻነቱ በታገለ ቁጥር የሐይማኖት አክራሪዎች፤ የቀድሞ ስርዐት ናፋቂዎች ወይም የግንቦት ሰባት ተከታዮች ናችሁ እያለ ቢያቅራራ እንዲህ አይነቱ የተለመደ የአምባገነኖች ቀረርቱ ያ የማይቀረዉ ክፉ ቀን ሲመጣ ስንቅ እንደማይሆነዉና ከህዝባዊ ቁጣ እንደማያድነዉ ከወዲሁ ሊገነዘብ ይገባል። ደግሞም ግንቦት 7 አላማዉ፤ ለህዝብ ያለዉ ክብርና ለኢትዮጵያ አንድነት ያለዉ ቀናኢነትና የማያወላዉል አቋም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በአጭር ግዜ ዉስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አስገኝቶለታልና የወያኔን የዕለት በዕለት አስተዋዋቂነት በፍጹም አይሻም።
ግንቦት 7 አላማዉና ፍላጎቱ እንደ ስሙ ፍትህ፤ ነጻነትና ዲሞክራሲ ነዉና የህዝባዊ ትግላችን አላማ ወያኔንና ዘረኛ ስርዐቱን መደምሰስ ብቻ ሳይሆን አገራችን ዉስጥ የህግ የበላይነት ሰፍኖ ኢትዮጵያ ዛሬም ነገም ከሽብርተኝነት የነጻች አገር አንድትሆን ነዉና ወያኔ ያሰኘሰዉን ቢናገር ወይም እንዳሰኘዉ ቢፎክር ንቅናቄያችን ከዚህ ህዝባዊ አላማዉ ንቅንቅ እንደማይል ለወገንም ለጠላትም ማረጋገጥ ይፈልጋል። ግንቦት 7 የኢትዮጵያና የህዝቦቿ ዋነኛ ጠላት ወያኔ ነዉ ብሎ ያምናል፤ ስለሆነም የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ክንድ ያነጣጠረዉ በዚሁ በዋነኛዉ የህዝብና የአገር ጠላት ላይ ብቻ እንደሆነ ኢትዮጵያዉያንና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ብልጽግና የሚመኙ ሁሉ እንዲገነዘቡለት ይፈልጋል።
ግንቦት 7 ህዝባዊ አላማ አንግቦ፤ ግብ አስቀምጦና ወዳስቀመጠዉ ህዝባዊ ግብ የሚያደርሰዉን የትግል ስልት በጥንቃቄ ነድፎ የሚንቀሳቀስ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ግንቦት 7 ወያኔና ዘረኛ ስርዐቱ ተደምስሰዉ ኢትዮጵያ በዜጎቿ ሙሉ ፍላጎትና ፈቃድ ብቻ የምትመራ አገር የመሆኗ ሀቅ የማይቀርና ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል ገድቦ ሊያቆመዉ የማይችል ህዝባዊ ማዕበል ነዉ ብሎ ያምናል። ግንቦት 7 በዚህ አጋጣሚ በየዋህነት ተሳስተዉና ግዜያዊ ጥቅም አታሏቸዉ ከሚንቋቸዉና እንደ ቤት ዉስጥ ዕቃ ከሚጠቀሙባቸዉ ዘረኞች ጋር እጅና ጓንት የሆኑ እንደ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አይነቶቹ የዋሆች የበደሉትን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዉ ህዝባዊ ትግሉን እንዲቀላቀሉ ወገናዊ ጥሪ ያቀርብላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግንቦት 7 ባለፉት ሁለት አመታት በተለይም ከወያኔዉ ቁንጮ ሞት በኋላ ከወያኔ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ዉስጥ የገባችሁ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና በድርጅቶቹ ዉስጥ የምትገኙ የኢትዮጵያ ህዝብ ወገኖች ወያኔን ለማስወድ ከዛሬ የተሻለ ግዜ አይመጣምና ኑና በጋራ ጠላታችን ላይ እንዝመት የሚል ህዝባዊ ጥሪዉን ያስተላልፋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
Thursday, November 7, 2013
ሀገራዊ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ!!!

በሶማሌ ክልል የኦብነግን ታጣቂዎች ቅስም ለመስበር ልጃገረዶችንና እናቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ጭምር በቤተሰብ ፊት በደቦ የሚደፍሩ፤ ለዚህ ተግባር የሠለጠኑ የልዩ ጦር አባላት መኖራቸው በስፋት የሚታወቅና በተደጋጋሚም የተዘገበ ጉዳይ ነው። ወያኔ፣ የኦጋዴን ወገኖቻችን በዚህ ጥቃት ተሸማቀው ያነገቡትን መሣሪያ ጥለው ፀጥ-ለጥ ብለው ይገዛሉ ብሎ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ዛሬ የሶማሌ ክልል ወንዱም ሴቱም፤ ወጣቱም አዛውንቱም በፀረ-ወያኔ አቋም የጋራ መግባባት ላይ ደርሷል። በኦጋዴን የወያኔ አስነዋሪ ጥቃት የፈጠረው ምሬት በውጭ አገራትም በሚደረጉ የፀረ ወያኔ ትግሎች የኢትዮጵያ ሶማሌ ተወላጆች ተሳትፎ እንዲጎለብት አድርጎታል። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በሶማሌ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በአፋር ክልልም ተመሳሳይ ጥቃት የዘወትር ትዕይንት እየሆነ መጥቷል። የአፋር የወል የግጦሽ መሬቶች ለሸኮራ አገዳ ልማት በሚል ሰበብ ሲነጠቁ የተቃወሙ የአገር ሽማግሌዎች ተደብድበዋል፤ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ተደፍረዋል። በአፋርም ውስጥ ለጾታዊ ጥቃት የሰለጠነ የወያኔ ልዩ ጦር ተሰማርቶ በሴቶች ብቻ ሳይሆን በወንዶችም ላይ አስነዋሪ ጥቃት አድርሷል። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
በጋምቤላ ውስጥ ወያኔ ወገኖቻችን ከፈጀ በኋላ በሕይወት የተረፉትም ቅስማቸውን ለመስበር ጾታዊ ጥቃት በመሣሪያነት ተጠቅሟል፤ አሁንም እየተጠቀመ ነው። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት በሁላችንም ላይ የደረሰ ነውና ቁጭታቸውን እንጋራለን። በጋምቤላ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ጥቃት ሀገራዊ ውርደት ነው።
የወያኔ ዝቅጠት ዘግናኝ ነው። ወያኔ ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ጾታዊ ጥቃት ያላደረሰበት የአገራችን ክፍል የለም። ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል … በሁሉም ቦታዎች ያልተነገሩ ጥቃቶች በዜጎታችን ላይ ደርሷል፤ እየደረሰም ነው።
በአንድ ወቅት በመሀል አገር፤ በሰሜን ሸዋ አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት በእብሪተኛ ወያኔ የተገደለውን ባለቤትዋን ብልት ይዛ አስክሬኑን እንድትጎትት መደረጉን ከዓይን እማኞች አንደበት ሰምተናል። በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሰበብ መስዋዕትነት እየተቀበሉ ያሉ ወገኖቻችን “ሽንታም አማራ” እየተባሉ ብልቶቻቸው ይቀጠቀጥ እንደነበር የሰማነው እና የምናውቀው ጉዳይ ነው። በወያኔ መዳፍ ውስጥ ውስጥ ገብተው በእስር ቤቶች በሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ ዘግናኝ ተግባራት እንደሚፈፀሙ መረጃዎች አሉ። በአዲስ አበባ በየቦታው ባሉት ስውር የማሰቃያ ቤቶችም ተመሳሳይ ተግባራት ዘወትር እንደሚፈፀሙ ይታወቃል።
ወያኔ ለጾታዊ ጥቃት ያሰለጠናቸው ሰዎችን በከተሞችም ውስጥ አሰማርቷል። በእነዚህ ጥቃቶች ግለሰቦች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ቢሆንም የተደፈርነው፣ የተዋረድነው ሁላችንም መሆናችን አጽንዖት ሊሰጠው ይገባል። የተደፈርነው እኛ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ነን። የተዋረደችው የምንወዳት አገራችን ኢትዮጵያ ነች።
ኢትዮጵያ አገራችን እፍረት ባልፈጠረባቸው ነውረኛ የወያኔ ዋልጌዎች እንድትገዛ እንድትረገጥ በመፍቀዳችን ጥፋቱ የኛም ጭምር ነው። ይህን ነውረኛ ቡድን በሥልጣን ላይ እንዲቆይ በፈቀድንለት መጠን በኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያችን ላይ የሚደርሰው በደል እየባሰ እንደሚመጣ በዓይኖቻችን እያየን በጆሮዎቻችን እየሰማን ነው።
ሰሞኑን በአንድነት ፓርቲ የምክር ቤት አባል ላይ የደረሰው ጥቃት የዚሁ አካል ነው። እኚህ ወገናችን የደረሰባቸውን ዘርዝሮ ለመናገር የሚከብድ መሆኑ ገልፀዋል። ማፈር የነበረባቸው ጥቃት አድራሾቹ መሆን ይገባቸው ነበር፤ ሆኖም ግን ይሉኝታ አልፈጠረባቸው። ምንም ይሁን ምን በወገናችን ላይ የደረሰው ጥቃት በእሳቸው ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን በሁላችንም ላይ የደረሰ መስሎ የሚሰማን መሆኑን ልንነግራቸው እንወዳለን። የተዋረደችው ኢትዮጵያ አገራችን ነች።
ይህ ውርደት እንዲያበቃ ወያኔ ከሥልጣን መወገድ ይኖርበታል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ “ወያኔን ከሥልጣን ማስወገድ” ቀዳሚ ሥራችን ነው የሚለው ኢትዮጵያን ለማዳን ከዚህ የሚበልጥ አንገብጋቢና አጣዳፊ ሥራ ስለሌለ ነው። ወያኔን ለማስወገድ እንተባበር።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
የኢንተርኔት አፈናንና ስለላን የሚፈቅደው አዋጅ ሀሙስ ይጸድቃል
ጥቅምት ፳፯(ሃያ ሰባት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ደንብ ቁጥር 250/2003 ሽሮ እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ ፤ ተጠሪነቱ ለጠ/ሚኒስትሩ የሆነ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ለማቋቋሚያ
የወጣው አዋጅ ሀሙስ ይጸድቃል።በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ተዘጋጅቶ በካቢኔ ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረጉ የትራንሰፖርት እና የኢንዱስትሪ የቁጥጥር ስርዓቶች ደህንነት ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረጉት የኢነርጂ፣ የባቡር ኔትዎርክ፣ የአቬሽን፣ የውሃ አቅርቦት ወዘተ የቁጥጥር ስርዓቶች ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል መደንገጉን ይገልጻል።
የሳይበርና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ደህንነት የሳይበር እና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች የኢንተርኔት ራዲዮ፣ ኢንተርኔት ቲቪ፣ የቲቪና የሬዲዮ አገልግሎቶች፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች፣ ዌብ ሳይቶች፣ ብሎጎች ወዘተ የሚያጠቃልል ሲሆን፤ ተደራሽነቱ ለሁሉም እኩል በመሆኑ
ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ካለው ፋይዳ በተቃራኒ ለጦርነት ቅስቀሳ፣ ለስም ማጥፋት ዘመቻ፣ የሃገርን ገጽታ ለማጉደፍ፣ ፀረ ልማት ፕሮፖጋንዳዎችን ለማሰራጨት፣ ፍርሃትንና አሉባልታን ለመንዛት፣ የኢኮኖሚ ስፔኩሌሽን ለማሰራጨት ወዘተ መጠቀሚያ ሊውሉ እንደሚችሉ ህጉ ይዘረዝራል።
ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረገው ወታደራዊ የእዝና የቁጥጥር ስርዓት ደህንነት በመላ ሃገሪቱ ዳር ድንበር ላይ የመሸገው የሃገር የመከላከያ ኃይል እየዘመነ መሄዱ እና ኮምፒዩተርን መሰረት
ባደረገው የእዝና የቁጥጥር ስርዓት ላይ መመራቱ ተገቢ እና አዋጪ መሆኑ አያከራክርም የሚለው አዋጁ፣ በመሆኑም ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረጉት መሰረተ ልማቶች ደህንነት መጠበቅ ማለት ወታደራዊው የእዝ እና የቁጥጥር ስርዓቱ ደህንነት መጠበቅ ማለት ነው ብሎአል። ይሁንና ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረጉ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ማንኛውም አደጋ በወታደራዊ የእዝ እና ቁጥጥር ስርዓቱ ላይ የሚደቀነው አደጋ መኖሩን የሚገልጸው አዋጅ፣ ይህ በብሄራዊ ደህንነት ላይ በቀጥታ የሚሰነዘር ጥቃት በአንድ በኩል ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረጉ መሰረተ ልማቶች በመጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ ኮምፒዩተርን መሰረት ያደረገው
ወታደራዊውን የእዝ እና ቁጥጥር ስርዓቱ በልዩ ሁኔታ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያትታል። አዲሱ ህግ መንግስት ዜጎቹ በኢንተርኔት የሚያደርጉትን ማንኛውንም አይነት ግንኙነት ለመቆጣጠር የሚያስችለው ሲሆን፣ የቴሌኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤትን ብቃት ለማሳደግ ከፍተኛ ባጀት እንደሚመደብም ያትታል።
Wednesday, November 6, 2013
ሰማያዊ ፓርቲ የክፍለ ሃገር መዋቅራት እየተገመገሙ ነው
November 5, 2013
ሰማያዊ ፓርቲ
በአዲስ አበባ ስኬታማ ሰላማዊ ተቃውሞዎችን በማድረግ ጉዞውን የጀመረው ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ ክፍላተ ሃገራት ያሉ መዋቅሮቹነ በመገምገምና አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ላይ ይገኛል፡፡በዚህም መሰረት ባለፈው እሁድ በ24/2/06 በሰሜን ሸዋ የሚገኙ ወረዳዎችን በደብረ ብርሃን ከተማ በመገኘት የገመገመ ሲሆን በእለቱም የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ በቦታው በመገኘት ስለ ፓረቲው አጠቃላይ ሁኔታና ጉዞ ገለፃ በማድረግ ስኬታማ ውይይት ከአባላት ጋር አካሂደዋል፡፡
በተመሳሳይም ከዛሬ ማክሰኞ 26/2/2006 አ/ም ጀምሮ ለ3 ቀናት በአርባ ምንጭ በወላይታ በአዋሳና ሆሳእና ከተሞች ላይ ከአባላት ጋር ውይይት የሚደረግ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም በሌሎች ከተሞች ላይ ውይይቱ የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል፡፡

Sunday, November 3, 2013
በኢትዮጵያ ውስጥ መቸቻልና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ እርቅና የሽግግር መንግስት ማቋቋም ቅድሚያ ሰጥተን ልንተገብረው የሚገባ ብቸኛው የቤት ስራቾን ነው።በማን አለብኝና በእብሪት የተሞላ የጠመንጃ አምልኮ ለአንዴና ለመጨረሻ ከታሪካቸችን መፋቅ አለበት። ኢትዮጵያ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩል የምታስተናግድ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ አገር ትሆን ዘንድ ከጥላቻና ከመጠላለፍ የዘር በሽታ ተላቀን ያለፈውን የታሪክ ምዕራፍ ፍፁም በሆነ ይቅርታና ፍቅር መዝጋት አለብን። የዛሬው የትናንቱን ሲኮንን፣ የነገው ደግሞ የዛሬውን እየኮነነ በድግግሞሽ የታሪክ ሽክርክሪት ውስጥ ከመኖር ወጥተን እውነተኛ ወንድማማችነት የሰፈነበት የፍቅርና የመቻቻል የፖለቲካ ባህል መገንባት ከቻልን አሁን የምናያት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከአደጉት አገሮች ተርታ በአኃዝ ሳይሆን በተግባር የምትሰለፍበት ቀን እሩቅ አይሆንም። ስለዚህ ጥላቻን፣ መነናቅን፣ ዘረኝነትን፣ ጠባብነትን፣ አስወግደን እንደ አንድ ህዝብ በጋራ ተሰልፈን ድህነትን ከአገራችን ለማጥፋት መረባረብ ይኖርብናል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
Subscribe to:
Posts (Atom)