Saturday, February 1, 2014
የመንግስት ባለስልጣናት የ7 ሚሊዮን ብር መኪና መግዛት ማቆም አለባቸው ሲሉ አፈ ጉባኤው ተናገሩ
ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አባ ዱላ ገመዳ ይህን የተናገሩት በዛሬ የፓርላማ ውሎ ላይ ነው። የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአገር ውስጥ የተመረቱ ምርቶችን መጠቀምና በ7 ሚሊዮን ብር የሚገዙ መኪኖችን መጠቀም ማቆም አለባቸው ብለዋል።
ኢሳት አዲስ አበባ መስተዳድር ሰሞኑን እጅግ ዘመናዊ መኪኖቹን በብዙ ሚሊዮን ዶላር ለባለስልጣነቱ ገዝቶ ማከፋፈሉን መዘገቡ ይታወሳል።
በሀረማያ ዩኒቨርስቲ በርካታ ተማሪዎች በፖሊሶች ተደበደቡ
ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው ማክሰኞ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት የዩኒቨርስቲ ግቢውን ለቀው በመውጣት ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ የፌደራል ፖሊስ በወሰደው እርምጃ የአንዲት ተማሪ ጆሮ መቆረጡንና በርካታ ተማሪዎች እጆቻቸውና እግሮቻቸው መሰበሩን ተማሪዎችና የዩኒቨርስቲው መምህራን ለኢሳት ገልጸዋል።
ችግሩ የተፈጠረው የውሃ ኢንጂነሪንግር ተማሪዎች የትምህርት ዘርፍ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው። ዩኒቨርስቲው የትምህርት-ዘርፍ ለውጥ እንደማያደርግ እና መማር የማይፈልጉ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣት እንደሚችሉ ማስታወቂያ መለጠፉን ተከትሎ፣ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው በሚወጡበት ጊዜ የፌደራል ፖሊሶች መንገድ ላይ በመጠበቅ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ደብደባ ፈጽመዋል።
በአሁኑ ጊዜ የውሃ ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ በፖሊሶች እየተጠበቁ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን አስተዳደር ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።